በንጋት ሐይቅ ለትውልድ የሚሸጋገር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሁለተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ንጋት ሐይቅ ረቂቅ ማስተር ፕላን ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነት እና ትብብር ጎልቶ የታየበት ነው።
ንጋት ሐይቅ ከአፍሪካ 4ኛው ግዙፉ ሰው ሰራሽ ሐይቅ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከ70 በላይ ደሴት የያዘ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ሐይቁ የኢትዮጵያን የዓሣ ምርት፣ ውኃ ትራንስፖርት፣ መስኖ ልማት፣ የቱሪዝም ዘርፍን ጨምሮ በርካታ ዘርፎችን በማጠናከር ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው ንጋት ሐይቅ ማስተር ፕላን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በውይይት መድረኩ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በአባዲ ወይናይ