Search

የአርሶ አደሩን ሕይወት እንደሚቀይር ተስፋ የተጣለበት የገጠር ኮሪደር ልማት

ማክሰኞ ጥቅምት 04, 2018 293

በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት እና ሞዴል መንደሮች የአርሶ አደሩን ሕይወት እንደሚቀይሩ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ነዋሪው ጤናማ እና አምራች ኃይል እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና መር በመሆኑ፣ ለታለመው ብልጽግና የገጠር ሽግግር ድልድይ እንደሚሆን ነው ያመላከቱት፡፡
ይህም ግብርናን መሰረት በማድረግ ወደ ኢንዱስትሪ የምንሸጋገርበት ድልድይ ነው ሲሉ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማት የገጠር አናኗርን የማሻሻል ዓላማ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ልማቱ በውስጡ በርካታ ነገሮችን መያዙን ጠቅሰው፤ የአካባቢውን አርሶ አደሮች እና ነዋሪዎች በተለያየ መልኩ ገቢያቸውን በማሳደግ እና አኗኗራቸውን በማሻሻል ተጠቃሚ እያደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
በዚህም ዘመናዊ አኗኗርን በመፍጠር ወደ ከተሞች የሚደረጉ ፍልሰቶችን መቀነስ እንደሚያስችል ነው ያመላከቱት፡፡
በሜሮን ንብረት