Search

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች ትግበራ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አረጋገጠ

ማክሰኞ ጥቅምት 04, 2018 58

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶች ትግበራ እያደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በቀጣይም በተለያዩ መስኮች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል።
በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በዓለም ባንክ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የፕሮጀክቶች ሂደት እና ለቀጣይ በሚኖሩ ዋና ዋና የትብብር ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
አቶ አሕመድ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ በማሳደግ ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና አንስተው፤ ለተደረገው እና በቀጣይም ለሚደረገው ከፍተኛ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ አመሥግነዋል።
ሰው ተኮርና ድህነት ቅነሳ ላይ እየተከናወኑ ስላሉ ውጤታማ ሥራዎች፣ በግብርና ምርታማነት፣ በኢነርጂ፣በሰብዓዊ ካፒታል ልማት እና በመሠረተ ልማት ዘርፎች የላቀ እገዛ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ንዲያሜ ዲዮፕ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለልማት እያሳየ ያለውን ቁርጠኛ አመራር እና አጠቃላይ ሂደት አድንቀዋል።
በመንግሥት ቁርጠኝነትም ሁሉን አቀፍ ማሻሻያ ፕሮግራም በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን ማሳካት መቻሉን አንስተዋል።
በቀጣይም የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት ዕቅዶች በተለያዩ መስኮች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህም መሠረት በኢነርጂ፣በግብርናና የአነስተኛ አርሶ አደሮች ምርታማነት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የእሴት ሰንሰለት ልማትን ለማሳደግ ዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ተነሳሽነትን እና የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ በሚሉት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድጋፉን እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ የልማት መርሐ ግብሮች፣ የሀገሪቱ የእድገትና የዘላቂ ልማት ዋና ዋና አንቀሳቃሾች በተሳካ ሁኔታ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የሁሉም አጋር አካላት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን በማረጋገጥ ለቀጣይ ትብብር ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል።