Search

የሰንበት ገበያዎች ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ምን እየተደረገ ነው?

ረቡዕ ጥቅምት 05, 2018 54

የቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት እና የኑሮ ጫናን ለመቀነስ ዓላማ አድርገው መጀመራቸው ይታወቃል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙት ገበያዎቹ አምራች እና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት፣ በአንድ በኩል ለአምራቾች የገበያ እድልን ሲፈጥሩ በሌላ በኩል ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡
በገበያዎቹ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች የሚቀርቡ ሲሆን አትክልቶች፣ ፍራፍሬዎች፣ የሰብል ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶች ማለትም እንደ ዘይት፣ ፓስታ፣ የዳቦ ዱቄት የመሳሰሉት ይቀርባሉ።
የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ታልሞ የተጀመረው ይህ የገበያ ሥርዓት ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ቢሆንም፣ በአንዳንድ የግብይት ሥፍራዎች ላይ የምርቶች ጥራት መቀነስ እና የዋጋ መጨመር በሸማቾች ላይ ቅሬታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
አንዳንድ ነጋዴዎች በንግድ ቢሮ ከተቀመጠው እና ከተለጠፈው የዋጋ ተመን በላይ በምርቶች ላይ ጭማሪ በማድረግ እንደሚሸጡ እና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን እንደሚያቀርቡ ሸማቾች ለኢቲቪ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ ኢቲቪ በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በንግድ ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑትን ስመኘው ተሾመን ጠይቋል፡፡
ኃላፊው በምላሻቸው የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎች ሸማቾች በተለይ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ታስበው የተቋቋሙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ስለመተግበሩ ቢሮው ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡
በምርት ጥራት እና በዋጋ ላይ የሚደረጉ ሕገወጥ ተግባራትን በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ ቢሮው የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ጥቂት ወራት በሕገ ወጥ ተግባር በተሰማሩ 149 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ አቅራቢ ነጋዴዎች ላይ ተገቢውን አሰራር በመከተል ከገበያ ትስስር እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ቁጥጥሩ በየጊዜው የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፤ ሸማቾች የንግድ ቢሮው ባስቀመጠው የዋጋ ተመን ብቻ በመሸመት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ሕገወጥ ተግባራትን ሲመለከቱም ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ