Search

በምርጫ መሸነፍ ለሀገራቸው የዴሞክራሲ ዕድገት ከመሥራት ያልገታቸው ራይላ ኦዲንጋ

ረቡዕ ጥቅምት 05, 2018 77

የዴሞክራሲ አቀንቀንቃኝ የነበሩት የቀድሞው የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ፣ በኬንያ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት እንዲያበቃ በማድረግ እና ሀገሪቱ አሁን የምትተዳደርበትን ሕገ-መንግሥት በመቅረፅ ውስጥ በነበራቸው ሚና በጉልህ ይጠቀሳሉ።

ለበርካታ አሥርት ዓመታት በገነቡት የፖለቲካ አመራር ችሎታቸው በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸውን በደማቁ ጽፈዋል፤ “የዘመናዊቷ ኬንያ አርክቴክት” ሲሉም የሚገልጿቸው አሉ።

በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት ታዲያ ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓትን በምትከተለው ሀገራቸው፣ ለፕሬዚዳንትነት ለአምስት ጊዜ ተወዳድረው ማሸነፍ ባለመቻለቸው ነው።

በእነዚህ ሁሉም ጊዜያት “ምርጫው ተጭበርብሯል” በሚል መሸነፋቸውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ እ.አ.አ በ2007 በተካሄደው ምርጫ “በሙዋይ ኪባኪ ተጭበርብሬያለሁ” ሲሉ ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ የተከሰተው ቀውስ በኬንያ ታሪክ ትልቁ እንደሆነ ይነገራል።

የያኔው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ችግሩን ለመቅረፍ የሥልጣን መጋራት ስምምነት እንዲፈፀም አደረጉ፤ ራይላ ኦዲንጋም በጥምረቱ መንግሥት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን አገኙ።

ራይላ ኦዲንጋ የሚታወቁበት አንዱ ባህሪቸው በምርጫ ከተሸነፉ እና ቅሬታ ካቀረቡ በኋላም ቢሆን ወደ ሥልጣን ከሚመጡት ፕሬዚዳንት ጋር እርቅ ለመፍጠር ያላቸው ቀናኢነት ነው።

በ2022ቱ የኬንያ ምርጫም ሽንፈት ቢያጋጥማቸውም አካታችነትን የመረጠውን የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶን መንግሥት የተቀላቀሉ ሲሆን አጋሮቻቸውም ዋና ዋና መንግሥታዊ ቦታዎችን መያዝ ችለዋል።

በኋላም የፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ራይላ ኦዲንጋ በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ድጋፉን ሰጠ። ራይላ ኦዲንጋ በቀጣናውም ከፍተኛ ድጋፍ የነበራቸው ቢሆንም በጠባብ ልዩነት በጅቡቲው ተወካይ ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ መሸነፋቸው ይታወሳል።

ራይላ ኦዲንጋ በሀገራቸው በተለይም የትውልድ አካባቢያቸው ከሆነ የምዕራብ ኬንያ ክፍል በርካታ ደጋፊዎች አሏቸው።

ደጋፊዎቻቸው “ባባ” (አባት)፣ “አግዋምቦ (የእግዜር ሥራ) እንዲሁም “ቲንጋ” (ትራክተር) /ራይላ በ1997 ለምርጫ ምልክትነት የተጠቀሙት ትራክተር በመሆኑ/ በሚሉ ቅፅል ስሞች ይጠሯቸዋል።

ራይላ አዲንጋ የስትራቴጂ ሰው እና ብዙኀንን በማንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ከታችኛው እርከን ማኅበረሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝነት በመፍጠር ችሎታቸው ስመጥር የሆኑ ሰው ነበሩ።

ለዴሞክራሲያዊ ነፃነት እና ለሰብዓዊ መብት ባላቸው የማይናወጥ አቋማቸውም ከሀገራቸው አልፎ በመላው ዓለም ለመታወቅ የበቁ ብርቱ ፖለቲከኛ ነበሩ።

በዚህ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ታዲያ ለእስር የተዳረጉባቸው ጊዜያትም በርካታ ቢሆኑም ለሀገራቸው የዴሞክራሲ ዕድገት ከመሥራት ግን አልገታቸውም።

እኚህ ብርቱ ፖለቲከኛ እና ለበርካቶች የፅናት ምሳሌ የሆኑት ሰው ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ80 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች በኅልፈታቸው የተሰማቸውን ኀዘን እየገለጹ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት የኀዘን መግለጫ፣ “በራይላ ኦዲንጋ ኅልፈት በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማኝን ኀዘን እገልጻለሁ” ብለዋል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #ebcdotstream #railaodinga