ኢትዮጵያ የአፍሪካን መጻኢ ዕድል የሚወስነውን አካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ24ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንደገለጹት፥ ኢትዮጵያ በመቶዎች የሚቆጠሩ አገልግሎቶችን ዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጧን እያሻሻለች ትገኛለች።
ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ የሆኑበት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም መዘርጋቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህም በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ መተማመንን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
"የዲጂታል ክፍያ ሥርዓታችን ባለፈው ዓመት ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ለማዘዋወር አስችሎናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።
ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በኩል በኮዲንግ እና በሌሎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎቶች ላይ ሥልጠና አግኝተው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውንም ጠቅሰው፤ እነዚህ ወጣቶች የነገዎቹ ፈጣሪዎች እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
"ከዚህ ልምዳችን የተማርነው አፍሪካ ለዲጂታል መሠረተ ልማት ትኩረት ሰጥታ ከሠራች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደምትችል ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #COMESA #Kenya #Ethiopia #AbiyAhmedAli