ኢትዮጵያ ቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ላይ በትኩረት እየሠራች መሆኑን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
ሚኒስትሯ ይህን ያሉት “ሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት 2025”ን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ነው።
ሁነቱ በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በአፍሪካ ክህሎት እና ፈጠራን በማሳደግ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት ወጣቶችን በቴክኖሎጂ ማስታጠቅ እንደሚገባ በመድረኩ ተነሥቷል።
የአፍሪካ ክህሎት ሳምንት ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ኢኖቬሽን እና ክህሎትን ለማጠናከር እንዲሁም አካታችና ጥራት ያለው የቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠናን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የክህሎት ሳምንቱ የመንግሥታት እና የግሉ ዘርፍ ትብብርን እንዲሁም አረንጓዴ ልማት እና ቴክኖሎጂን ለማበረታታት ሚናው የጎላ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።
ወጣቶች አፍሪካን የሚገነቡ የፈጠራ ሐሳቦችን በማፍለቅ እንዲሠሩ ለማድረግ በቴክኒክ እና ሙያ ትምህርት እና ሥልጠና ላይ በቁርጠኝነት መሠራት እንዳለበት በመድረኩ ተነሥቷል።
ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ሥራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት እንዲሁም በቴክኖሎጂ፣ በፖሊሲ እና በአሠራር በመደገፍ አጀንዳ 2063 እንዲሳካ ዘርፉ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
ዛሬ በይፋ በተከፈተው ሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት 2025 መድረክ ላይ የ10 ዓመት የአፍሪካ ልማት ስትራቴጂም ይፋ ተደርጓል።
በብሩክታዊት አስራት
#EBC #ebcdotstream #MoLS #AfricaSkillsWeek #Skills