ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪኳ በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካን ወክላ መቆም የቻለች ሀገር መሆኗን የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሲመሰረቱ ቀዳሚ መሆኗን አንስተው፤ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ከመስራች እና ቀዳሚ አባላት ተርታ እንደምትጠቀስ ፕሮፌሰር አህመድ አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ብቻ ሳሆን ከሁሉም ሀገራት ጋር ወዳጅ መሆኗን ጠቅሰው፤ ከቀደምት ታሪኳ በመነሳት ወገንተኛ መሆን ብትፈልግ እንኳ አትችልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ከጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች ጋር የደም ትስስር ያላቸው መሆኑን አንስተው፤ ይህም ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጥሩ አግዟቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን እየተገበረችው የምትገኘው ጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በንግድ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በባህል ልውውጥ፣ በጋራ ሰላም ጉዳይ ላይ በትብብር በመሥራት ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት ትስስርን ከማጠናከራቸው ባሻገር ዲፕሎማሲውን እያጎለበቱት እንደሆነም ነው የገለጹት።
በቱርክ አደራዳሪነት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በቅርቡ የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ውጤት ተደርጎ እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የምታከናውናቸው ተግባራት ማሳያ ነው ብለዋል።
የሰላም ዘብ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም ለቀጣናው መረጋጋት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ እንደሚገኝ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ ተነግረዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#ebcdotstream #ethiopia #diplomacy