Search

ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ለማፅናት እየሠራ ያለው ቀጣናዊ የጋራ ገበያ:- ኮሜሳ

ሓሙስ መስከረም 29, 2018 88

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በናይሮቢ፣ ኬንያ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች ዕድገት ማዋል” በሚል ጭብጥ በተካሄደው 24ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (COMESA) የመሪዎች ጉባዔ ተሳትፏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ጉባዔውን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ፥ እንደ ኮሜሳ ያለው ቀጣናዊ አደረጃጀት ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጣና በመፍጠር በመካከላቸው የዕቃዎች እና የአገልግሎቶች ዝውውርን የሚያሳልጡበት ነው ብለዋል።

ማኅበረሰቦች ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን በነፃ ማዘዋወር በቻሉ ቁጥር በመካከላቸው ሊፈጠር የሚችለው ግጭት እየቀረ፣ ከፉክክር ይልቅ በትብብር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት  የሚዳብርበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል።

እንዲህ ያለው ቀጣናዊ የጋራ አደረጃጀት የሸቀጦች ብቻ ሳይሆን የሰዎች ዝውውርም ነፃ ሆኖ የአንድ ሀገር ዕድገት የሌላው ሀገር ዕድገት የሚሆንበት፣ ከፉክክር ይልቅ በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተ አብሮ የማደግ እሴት የሚዳብርበት ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ኮሜሳም በቀጣናው ሀገራት መካካል የንግድ ትስስር ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ብዙ ርቀት የተጓዘ ጥምረት እንደሆነ አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል። 

ጉባዔው ሀገራት የዲጂታል ሥርዓት የእሴት ሰንሰለትን የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው አማራጮች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ አፅንዖት ስለመስጠቱም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

በሃይማኖት ከበደ

#ebcdotstream #COMESA #Nairobi #Ethiopia