Search

የገጠር ኮሪደር ልማት ከግብዓት እስከ ገበታ ያለውን ሰንሰለት ምቹ የሚያደርግ ነው

ሓሙስ ጥቅምት 06, 2018 111

የገጠር ኮሪደር ልማት መንደሮች ከግብዓት እስከ ገበታ ያለውን የአርሶ አደሩን የእሴት ሰንሰለት ምቹ እና የተሟላ የሚያደርግ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር ገለፁ።
ኃላፊው ከኤፍ. ኤም 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ የአርሶ አደሩን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያው ተጠቃሚነት የሚያዳብረው የኮሪደር ልማት፤ የመደመር እሳቤን ልምምድ እያሳደገ የሚሄድ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን የሚያደርግ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የቤተሰብ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ እንዲሁም የማህበረሰብ ብልፅግናን በጊዜ ሂደት የሚያሳካ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የገጠሩን የኑሮ ዘይቤ እየቀየረ ያለው የገጠር ኮሪደር ልማት ከኑሮ ማዘመን ባሻገር የእንስሳት እና የተፈጥሮ ግብዓትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።
በገጠር ኮሪደር ልማት በሚፈጠረው የላቀ ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል እና የመሰረተ ልማት መሳለጥ ድምር ውጤት የሀገር ብልፅግና ይፋጠናል ሲሉም ገልፀዋል።
የሀገሪቱን ገጠራማ አካባቢዎች ማዘመን የተረጋጋ የገቢ ምንጭ፣ ጤናማ ማህበረሰብ፣ ዘላቂ ምርታማነት እና ውጤታማነትን ከማስረፅ አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በሴራን ታደሰ