ኢትዮጵያ በውኃ የተከበበች፤ ሕዝቧ ግን የባህር በር የተነፈገ ነው ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
የኢትዮጵያ ሕዝብ “ሰለ ቀይ ባህር አንናገርም፣ አናነሣውም፣ ጉዳዩ ከተነሣም ለግጭት ነው” በሚል የተሳሳተ ትርክት ሕጋዊ መብቱን አጥቶ ቆይቷል፤ ያ ሰህተት የመታረሚያ ጊዜው ታዲያ አሁን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ “እኛ ግጭት አንፈልግም፤ ነገር ግን ስለ ቀይ ባህር እናነሣለን” ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የምትገኘው በቀይ ባህር እና ዓባይ ውስጥ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ይህኛው ውኃ ይመለከትሻል፤ ይህኛው ውኃ ደግሞ አይመለከትሽም" ልትባል አይገባም፤ ተፈጥሮ እንደዛ አይልም ሲሉ ነበር የገለጹት።
ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ቀጣና በመጠቆምም ሌሎች የቀጣናው ሀገራት ስለ ዓባይ ወንዝ እና ስለ ቀይ ባህር የይገባኛል ጥያቄ እያነሡ ኢትዮጵያ ግን የቀይ ባህር ጥያቄ እንዳታነሣ የሚያደርጉት ሙከራ ፍትሐዊነት የጎደለው ሰለመሆኑም አብራርተዋል።
"ለሌሎች ሀገራት ዓባይ ኅልውናቸው እንደሆነ ሁሉም ሰው ይናገራል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የቀይ ባህርን ጉዳይ በፓርላማ አባላት ደረጃ እንኳን መወያየት እንደ ነውር ሲታይ መቆየቱ እንደሚያሳምማቸው ገልጸዋል።
“በራሳችን ዓባይ እና በራሳችን ሕዳሴ ላይ ባገኙት መድረክ ሁሉ እንደፈለጉ እየተናገሩ እኛ ስለ ቀይ ባህር እንዳንናገር ሊያደርጉ አይችሉም” ሲሉም ነው ያሰመሩበት።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ቀይ ባህር እና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ፤ ለኢትዮጵያ ዕድገት ወይም ጥፋት መሠረት ናቸው።
በመሆኑም በቀይ ባህር ጉዳይ ላይ ልክ እንደ ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ድርድር ለማድረግ መንግሥታቸው ዝግጁ መሆኑን፣ ድርድሩ ግን ‘በቀይ ባህር አትጠቀምበት' የሚል እስካልሆነ ድረስ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚ እና በዘር (ethnic) ሕጋዊ የቀይ ባህር ጥያቄ አላት የሚል ስምምነት ስለመኖሩም ጠቅሰዋል።
"የቀይ ባህር ጥያቄ ሳናነሣ ለብዙ ጊዜያት ተቀምጠናል፤ አሁንም ለምን ዝም አንልም? ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቢያጋጨንስ" የሚል ስጋት የሚያነሡ አካላት እንዳሉ ጠቁመው፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 50 ሚሊዮን እንደነበር እና አሁን በቅርቡ 150 ሚሊዮን ለሚሆን ሕዝብ ግን የጂኦግራፊ እስረኛ ሆኖ መኖር እንደማይችል በአመክንዮ አብራርተዋል።
ይህ ሁሉ ሕዝብ ድህነት ውስጥ ሆኖ መኖር በእጅጉ እንደሚከብደው እና በተፈጥሮአዊ ሂደት ወደ ሆነ ቦታ እንደሚበተን፤ ያ እንዳይሆን መውጫ ወይም መተንፈሻ እንደሚፈልግ ነው የገለጹት። ለዚህ ደግሞ መነጋገር እና መልክ ማስያዝ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሐቀኛ እና ሕጋዊ የሆነው የባህር በር ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኝበት ወሳኝ ጊዜ ላይ መድረሱን ነው የገለጹት።
በዮናስ በድሉ