የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በIMF እና ዓለም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን በስብሰባዎቹ ለመሳተፍ ከተገኙ ዓለም አቀፍ ከፍተኛ ባለሀብቶች ጋር በዋሽንግተን ዲሲ በመገናኘት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ የፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን አካሂደዋል። 
ስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ በተሰኘው ተቋም የተዘጋጀው ይህ የባለሃብቶች የውይይት መድረክ ከአውሮፓ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ታዋቂ ባለሀብቶችን ያካተተ ነው።
ውይይቱ በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ሐሳብ እንዲለዋወጡ ያስቻለ መድረክም ነው።
የብሔራዊ ባንክ ገዥው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን በመወከል ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጅ ልዩ መድረክ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ የሪፎርም ሥራዎች፣ የዕድገት ሁኔታ እና እምቅ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ባዳሰሰ መልኩ ሰፊ ማብራሪያዎችን አቅርበዋል።
በውይይቱ ወቅት ዓለም አቀፍ ባለሃብቶቹ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ማንሳታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ጠቁሟል።
ከተነሡት ጥያቄዎች መካከል የኢትዮጵያን የዕድገት አቅጣጫ፣ የዋጋ ንረት፣ የክፍያ ሚዛን፣ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ እና የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ያተኮሩት ይጠቃሉ።
ዶክተር ኢዮብ የተነሡ ጥያቄዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስቀጠል፣ የፋይናንሺያል ሴክተሩን ለማዘመን እና የባለሃብቶችን እምነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያካሄዳቸው ያሉትን ሰፋፊ ጥረቶች በመዘርዘር አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች ዙሪያ ለባለሀብቶቹ ሰፋ ያለ የግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የሪፎርም ሥራዎች የዋጋ እና የውጭ ምንዛሬ መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋፋት እና በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ሥርዓትን ለማራመድ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ እና የተስተካከለ የሒሳብ አያያዝን በመጠበቀም እና ቀስ በቀስ የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ ላይ ያተኮረ፣ ጠንካራ እና ሰፋ ያለ ዕድገትን እየደገፈ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የነበረው የውይይት ጊዜ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሰፋፊ የሪፎርም አጀንዳዎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ዓላማ ያደረጉ፣ ቁርጠኝነትን የሚያረጋግጡ እና በፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማኅበረሰብ መካከል ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ወሳኝ መድረክ ሆኖ አገልግሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዘንድሮው የIMF እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ የፖሊሲ ግልጽነትን ለመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ ያስገነዘበበት መድረክ እንዲሆን ማድረጉን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል።
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            