ከዓመታት በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያሉ በ20 ብር የጀመሩትን ቁጠባ እና የሥራ ሃሳብ ወደ ተግባር የቀየሩት ወጣቶች ዛሬ ላይ ካፒታላቸውን ወደ 60 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችለዋል።
ዛሬ ላይ የኤግዞዳስ ፋርም ማኅበር አባል የሆኑት ወጣቶቹ የለውጥ ተሞክሯቸውን ለብዙዎች እያካፈሉ ይገኛሉ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘው ይህ ማኅበር ባሳየው ለውጥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮች እና ኢንተርፕራይዞች ልምድ በማካፈል ላይ ነው።

የማኅበሩ አባላት በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ተማሪ እያሉ የቆጠቡትን 60 ሺህ ብር እና ፕሮፖዛል ይዘው ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ ያመራሉ።
በወቅቱ ከነበረው ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተጨማሪ 300 ሺህ ብር የብድር ድጋፍ አግኝተውም ወደ ሥራ ይገባሉ።
በአሁኑ ሰዓት ያገኙትን ብድር ከመመለስ አልፈው ካፒታላቸውን 60 ሚሊዮን ብር ያደረሱት ወጣቶቹ፤ ለ107 ቋሚ ሠራተኞችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

የማኅበሩ መስራች እና ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ተረፈ ስምኦን፥ በአጭር ጊዜ ለተመዘገበው ለውጥ አስተሳሰብ ላይ መሥራት ዋነኛው የስኬት መንገድ ነበር ይላሉ።
በማኅበሩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም በጊዜ ሂደት የተመዘገበው ለውጥ አስደናቂ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለውጥ ከትንሽ እንደሚጀምር መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገር ማኅበሩ በከፈተው ኮሌጅ በ2 ዙር ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ኮሌጁ በአሁኑ ሰዓት የሲኦሲ ምዘና ማዕከልም ጭምር ነው።
በተጨማሪም ማኅበሩ ዶሮ፣ ወተት እና የወተት ተዋፅዖዎችን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
በተመስገን ተስፋዬ
#ebcdotstream #entrepreneurship #saving #business
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            