ኢትዮጵያ የምትገነባው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ሀገሪቱ ከማዳበሪያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ሊደርሱባት የሚችሉ ጫናዎችን እንድትቋቋም አቅም የሚሰጣት ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገለጹ።
አቶ አዲሱ ከኢቢሲ ኤፍ.ኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደርጉት ቆይታ፥ የተለያዩ ሀገራት ከምግብ ዋስትና ባሻገር ሉዓላዊነትን እና የላቀ ምርታማነትን ማረጋገጥ የቻሉት መሰል የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የምትገነባው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካም ግንባታው ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ የሀገሪቱን የግብርና ምርት እና ምርታማነት እንደሚያልቀው ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሳ ፈይሳ በበኩላቸው፥ የሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረውን የማዳበሪያ አቅርቦት ለማሳደግ ቁርጠኛ እርምጃ መወሰዱ ምርታማነትን የሚያሳልጥ ስለመሆኑ ነው የተናገሩት።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው እየጨመረ የመጣውን የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት የሚያረካ እና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋገጥ ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምህሩ ሞኬ ናቸው።
በሌላ በኩል የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታው ፕሮጀክት መጀመር አዲስ ተስፋ የፈጠረባቸው አርሶ አደሮች፥ ይህ ጅማሮ ለተሻለ ምርታማነት ተነሳሽነትን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
አክለውም፥ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው በሕዳሴ ግድብ ላይ ያየነውን የመንግሥት ቁርጠኝነት እና የሕዝብ አንድነት ይበልጥ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በሴራን ታደሰ
#ebcdotstream #ethiopia #godefertilizerproject