በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከዓለም ባንክ እና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ለአዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፋይናንስ ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን አመራሮች ጋር በዋሸንግተን ዲሲ ተወያይቷል። 
ልዑኩ ለአዲሱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ብድር ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተወያየ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን አመራሮች በአዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው በማረጋገጥ ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ለሚያደርጉ የኢንቨስትመንት ዋስትና ለመስጠት፣ የአሜሪካ የግል ድርጅቶች በአጋርነት በግንባታው እንሳተፋለን ብለዋል።
በአፍሪካ በዓይነቱ ግዙፍ የሆነው የቢሸፍቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብልፅግና መረጋገጥ እንዲሁም የቀጠናውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ኮርፖሬሽኑ በፕሮጀክቱ ለማሳተፍ ያሳየውን ፍላጎት በአዎንታ እንደሚቀበሉት አረጋግጠዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ላይ የጋራ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን ማኅበረሰብን የሚጠቅሙ እና በሥራ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያሚጡ ኢንቨስመንትን ለማሳደግ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።
ሁለቱ አካላት ለቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፋይናንስ ለማፈላለግ በቀጣይም ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መድረሰቻውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በላሉ ኢታላ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            