የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ማርዬታ ዬገር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ስትራቴጂካዊ ክልላዊ መሠረተ ልማት ኮሪደሮች ትብብርን ማጠናከር፣ በሂደት ላይ ለሚገኙ የሪፎርም መርሃ-ግብሮች ድጋፍ ማድረግ እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የመንግሥት የትኩረት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን አድርገዋል።
ሚኒስቴሩ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የዓለም አቀፍ አጋርነት ዳይሬክተር ቶራያ ትሪኪ ጋር ባደረጉት ውይይት ደግሞ ባንኩ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳዎች በተለይም እንደ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ፣ ውኃ፣ ሳኒቴሽን እና ንጽህና እንዲሁም የሴቶች የሥራ ፈጠራ ልማትን ለመሳሰሉ ተግባራት ለሚያደርገው ተሳትፎ እና ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ቀጣዮቹ የባንኩ የድጋፍ አቅጣጫዎች ለአካታች እና ዘላቂ የገጠር ኢኮኖሚ ልማት ኢኒሼቲቭ እና ለማኑፋክቸሪንግ ሴክተር የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደሚሆኑም ዘርዝረዋል።
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በበኩሉ ለሦስተኛው ምዕራፍ የገጠር ፋይናንስ ፕሮግራም (RUFIP III) የ110 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
የገጠር ፋይናንስ ፕሮግራም ለገጠሩ አካባቢ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማስፋት፣ የፋይናንስ አሳታፊነትን ማጎልበት እና ሰፊውን የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጥረትን ለመደገፍ ያለመ ነው።
ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት እና የአውሮፓ ኅብረት ተቋማት ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ የግሉ ዘርፍ ዕድገትን ለማጎልበት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ያላቸውን አጋርነት የሚያንፀባርቅ ስለመሆኑ ተገልጿል።
በዮናስ በድሉ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            