Search

የተፈጥሮ ጋዝ - አስፈላጊው የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሀብት

ዓርብ ጥቅምት 07, 2018 75

ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብቶቿን ከቀድሞው በተሻለ መንገድ እያለማች ወደመጠቀሙ ተሸጋግራለች፤ በተለይ የተፈጥሮ ጋዝ ሌላኛው የኢኮኖሚ አቅም ማሳደጊያ መሆኑ ይገለፃል።
የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) በኢቢሲ ዳጉ ላይ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ በርካታ ሀገራት ከድህነት የወጡት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ተጠቅመው ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያም የከርሰ ምድር ሀብቷን በስፋት ለመጠቀም የሚያስችሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን መጀመሯ ለእድገቷ መነሻ እንደሚሆናት ጠቁመዋል፡፡
የሥራ እድል ለመፍጠር እና ከድህነት ለመውጣት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቁ ሥራዎች መከናወን እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለሀገሪቷ እድገት አስፈላጊ ኢንቨስትመንት መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
እያደገ የመጣው ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የኃይል አቅርቦት ለመሸፈን፣ በቅርቡ ግንባታው የተጀመረው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ትልቅ ሚና እንደአለውም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያችል መሆኑንም አመላክተው፤ ይህም የኃይል አማራጭን እንደሚያሳድግ ነው ያስረዱት።
በ2017 ዓ.ም ብቻ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው 4.3 ቢሊየን ሊትር ነዳጅ ውስጥ አብዛኛው ለተሽከርካሪዎች ፍጆታ የዋለ ቢሆንም 8 በመቶው ለኢንዱስትሪ አገልግሎት መዋሉን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ወደሥራ ያስገባችው የተፈጥሮ ጋዝ እና ሁለተኛ ዙር ፕሮጀክቱ የኃይል አቅርቦት አማራጭን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚቀንስ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የገለፁት፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ