የኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ባሕር በር ባለቤትነት እያራመደው ያለው አቋም ትክክለኛ ነው ሲል አርቲስት ቀመር የሱፍ ገልጿል።
ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 “መሰንበቻ” ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረገው አርቲስት ቀመር፥ ኢትዮጵያ የባሕር በር አጥታ መቆዘም የለባትም ብሏል።
እርሱም የዚህ ሀሳብ ተጋሪ በመሆኑ ከሥራ ባልደረባው ዮሰን ጌታሁን ጋር በመሆን ስለባሕር በር አስፈላጊነት የሚያወሳ በአፋን ኦሮሞ የተዜመ ‘ገላኖ’ (GALAANOO) የሚል ሙዚቃ ለአድማጭ ጆሮ ማድረሱን ተናግሯል።
ሙዚቃውም በአጭር ጊዜ ተወዳጅነትን ማትረፉን የገለጸው አርቲስቱ፤ በቀላሉ ሊወደድ የቻለውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚቆጭበት እና ሊሰማው የሚፈልገው ርዕሰ ጉዳይ በመሆኑ ነው ይላል።
ከዚህ ቀደም በግብፅ ሀገር የተወሰነ ቆይታ እንደነበረው ያነሳው ቀመር፥ በአንድ ወቅት በሬስቶራንት ውስጥ ውኃ አዝዞ ከጠጣ በኋላ "የጠጣሁት ውሃ የእኛ ነው፤ አልከፍልም" በማለቱ ለእስር የተዳረገበትን ገጠመኝ አጋርቷል።
"ግብፆች ከዓባይ ባገኙት ውኃ አስዋን ግድብን ሠርተው ከተሞቻቸው 24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያገኙ በመመልከቴ የእኛ የበይ ተመልካችነት ያስቆጨኝ ነበር" ብሏል።
"በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሳካነውን ድል በባሕር በርም መድገም አለብን" የሚለው አርቲስት ቀመር፤ አይቀሬ በሆነው ሀገራዊ አጀንዳ ላይ እርሱን ጨምሮ የሙያ አጋሮቹ የዜግነት ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመላክቷል።
በተለይ በኦሮምኛ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው እና በሥራዎቹ ብዙ አድናቂዎችን ያፈራው ቀመር የሱፍ ስለ ፍቅር፣ ስለ ናፍቆት እና ስለ ባህል አዚሟል።
በባሕር በር ቁጭት በቅርቡ በሠራው Galaanoo (ገላኖ) በተሰኘ ዜማውም ተወዳጅነትን አትርፎበታል።
በሲሳይ ደበበ
#ebcdotstream #seaport #GERD #kemeryousuf