Search

የሉዓላዊነት ዓርማ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል

ሓሙስ ጥር 14, 2018 242

አኩሪ የጀግንነት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ከምስረታው ጀምሮ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበርና ሕዝብን በማገልገል ላይ ይገኛል።
ዘጠኝ አሥርት ዓመታትን የተሻገረው ይህ አንጋፋ ተቋም፣ ዛሬም ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ ይገኛል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተቋሙ ግንባታ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ አየር ኃይሉ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ ዘመናዊነትን ተላብሶ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ ነው።
ተቋሙ 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን "የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ያከብራል።
የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ከኢቲቪ "አዲስ ቀን" መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ የአየር ኃይል ተዋጊ በራሪ፣ የሴፍቲ ዲቪዥን ኃላፊና ኢንስትራክተር ኮሎኔል ተዘራ በቀለ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ኩራት መሆን የቻለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
 
አየር ኃይሉ በአሁኑ ወቅት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚያስችል ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሻለቃ ሰኢድ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በቀኝ ግዛት ቀንበር ሥር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ የራሷን አየር ኃይል ማቋቋም መቻሏን አንስተዋል።
አየር ኃይሉ ባለፉት 90 ዓመታት ውስጥ በርካታ ድሎችን በመጎናጸፍ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የገለጹት።
ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ባላቸው ባለሙያዎቹ የሚታወቀው አየር ኃይሉ፤ ከጊዜው ጋር የሚጓዝ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማሰማራት አሁን ላለበት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ መድረስ መቻሉን አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የኢትዮጵያን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
 
በሜሮን ንብረት