ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተከላከለችበት መንገድ ማንኛውንም ሥነ ሕይወታዊ ስጋት በብቃት መመከት እንደምትችል ያሳየ መሆኑን የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ማጥፋት ችላለች።
በዚህም ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በመከላከል በጥቅምት ወር ተከስቶ የነበረውን የማርበርግን ቫይረስ ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የእውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር ተካሂዷል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዥያን ካሴያ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ጠንካራ ርምጃ ወስዳለች።
ኢትዮጵያ ንቁ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ያስመዘገበችው ውጤት መሆኑን በማንሳት፣ ይህም ጠንካራ የበሽታ መከላከል አቅም እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ የሆነችበት መንገድም የጠንካራ አመራር ብቃት ማሳያ መሆኑን አመልክተው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ትክክለኛና ዘመኑን የዋጀ ተግባር ማከናወኗን ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ጥበብና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተገኘው ስኬትም ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታ መከላከል ግብረ ኃይል ጋር በትብብር ሲሰራ እንደነበርም ተናግረዋል።
በዚህም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።

ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማንሳት፤ ለኢትዮጵያ የበሽታ መከላከል ስርዓት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፍራንሲስ ካሶሎ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ በሽታ ነፃ የሆነችበት መንገድ የመንግሥትና የማኅበረሰቡ ትብብር ውጤት መሆኑን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።
በሽታው በዓለም ላይ በፍጥነት እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት በኢትዮጵያ ባለው ግልፅና የተቀናጀ የበሽታ መከላከል ስርዓት ቫይረሱን ማጥፋት ተችሏል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በመንግሥት፣ በጤና ተቋማትና በማኅበረሰቡ መካከል የነበረው የትብብር እርምጃ በተግባር ለውጥ ማምጣቱን አይተንበታል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ ወቅቱን በጠበቀ ብሔራዊ ትብብር የመጣ ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ የማርበርግ ቫይረስ መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ዘርፎች በጋራ ሲሰሩ እንደነበር በማስታወስ፤ ትብብራቸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች፤ ኢትዮጵያ ቫይረሱን ለመከላከል ያደረገችው ጥረት ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሚሆን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንግሊዝ በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም በሽታን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አምባሳደሩ አስታውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር ጠንካራ ምላሽ መስጠቷን ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ ተምረናል ያሉት አምባሳደር ሴም፤ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል፡፡