ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ደባ እና በባንዳዎች ሴራ ያጣችውን የባህር በሯን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስመለስ የተጀመረው ጥረት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚደገፍ መሆኑን የቀድሞ የባህር ኃይል አባል ፒቲ ኦፊሰር ፈረደ ፍትሐነገስት ተናገሩ።
ከ1972 እስከ 1983 ዓ.ም ለ11 ዓመታት በኢትዮጵያ የባህር ኃይል ውስጥ በፒቲ ኦፊሰርነት ማዕረግ በመርከበኛነት ያገለገሉት አቶ ፈረደ ፍትሐነገሥት ከኢቢሲ ዶትስሪም ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያን ከ500 እና 600 ዓመታት በላይ በቀይ ባህር የነበረንን የባህር በር ለ30 ዓመታት ማጣታችን ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል ብለዋል።
በባህር በር እጦት ምክንያት ለሀገር ደኅንነት እና ሉዓላዊነት አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን ከውጭ በነፃነት እና በምሥጢር ማስገባት አለመቻል፤ በቀይ ባህር ዙሪያ ላይ የነበረንን የበላይነት ማጣት፤ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ከውጭ ለማስገባት ለወደብ ኪራይ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋችን ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እና ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለባት ሀገር፣ የባህር በርን በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ብቻ እያየች የባህር በር እንዳትጠቀም አድርጎ ማቆየት ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገሮች ሰላም ማጣት ጭምር ምክንያት ይሆናል ይላሉ።
የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስፈፀም መሥዋዕትነት መክፈል ይጠበቃል፤ ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግሥት ጋር ሊቆም ይገባዋል በማለት መክረዋል።
መንግሥት ከጉልበት እና ከጦርነት ውጪ በሆነ መልኩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት የማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል።
ጥያቄው የጎረቤት ሀገራት የቤት ሥራ ጭምር ነው ያሉት አቶ ፈረደ፣ በሰጥቶ መቀበል ፖሊሲ ጥያቄው እንዲመለስ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያ ባህር በር እንደነበራት ብዙ ሊነገረው እና ብዙ ሊያውቅ፣ በብዙም ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
የባህር በር እንደ ሀገር ሉዓላዊነታችን ሊከበር የሚችልበት፣ ብዙ የሥራ ዕድሎችን ልንፈጥር፣ በርካታ ሠራተኞችን ልናፈራ፣ ኢኮኖሚያችንን ልናሳድግ የምንችልበት ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ትውልዱን ማንቃት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የባህር በር ጥያቄን ለመመለስ መንግሥት በሕጋዊ እና በሰላማዊ መልኩ ጠንክሮ እንዲሄድ ሕዝቡ የእኔነት ስሜት በመፍጠር ግፊት እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
በላሉ ኢታላ