የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በሀገሪቱ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ባለድርሻ አካል ሊሆኑ እንደማይገባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሊቀ መንበሩ በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በቀይ ባሕር የባሕር በር ጥያቄ እና በምርጫ 2018 ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ቀይ ባሕር ያለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድ በፖለቲካ ሴራ ያጣነው ተፈጥሯዊ ሀብታችን ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህን ታሪካዊ ሀብት ማጣት በአሁኑ ትውልድ ዘንድ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት የፈጠረ በመሆኑ፣ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን ሀገራዊ አጀንዳ አድርጎ ማምጣቱን አብን በአዎንታ ይደግፈዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ባለቤትነት በሴራ እንድታጣ መደረጉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ በደል መሆኑን የጠቀሱት ሊቀ መንበሩ፤ አብንም ይህንን ፍትሐዊ ጥያቄ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ ተጠቃሚነቷን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንዳረጋገጠችው ሁሉ፣ በባሕር በር ጥያቄ ላይም በጋራ መሥራት እንደሚገባ በለጠ ሞላ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አሳስበዋል።
ታሪካዊ ጠላቶች የኢትዮጵያ የልማት ጥረት እንዲደናቀፍ ሌት ተቀን ቢሠሩም፣ ኢትዮጵያውያን ሴራቸውን በፅናት ሊመክቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከብሔራዊ ጥቅም እና ስትራቴጂካዊ የባሕር በር ጥያቄ በላይ ትኩረት የሚሰጠው ሌላ ምንም ዓይነት አጀንዳ እንደሌለ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)አረጋግጠዋል።