በሶፍኡመር ዋሻና ሎጅ ፕሮጀክቶች አካባቢ የቱሪስት አገልግሎት መስጫ የባቡር መስመር ተገንብቷል።
የባቡር መሰረተ ልማቱ በአካባቢው ያለውን የቱሪስት መስህብና መልከዓ ምድር ለመጎብኘት እንዲያመች ተደርጎ መሰራቱን የኢትየጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ህሊና በላቸው (ኢ/ር) ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም የተሰራው ባቡር ሌሎች የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን አቅም የተፈጠረበት መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያዊያን መሐንዲሶች አቅም የተሰራው የቱሪስት አገልግሎት መስጫ ባቡር በውስጡ 50 ሰዎችን ማስቀመጥ የሚያስችል እና 10 ሰዎች ከላይ ሆነው መልከዓምድሩን ለማየት እንዲችሉ ተደርጎ ተሰርቷል።

የሶፍኡመር ሎጅን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ እየተዘረጋ ያለው የባቡር መሰረተ ልማት የመጀመሪያ ምዕራፍ 2 ኪ.ሜ ግንባታ ተጠናቅቋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ቀጣይ ዙር የባቡር መስመር ግንባታም እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ በፊት የባቡር ሀዲድ ማንጠፍ በውጭ አቅም ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ እንደነበር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ አሁን ላይ ግን ዲዛይን ከማድረግ ጀምሮ ያለው ሥራ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የተሰራው ሥራ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችን፣ የግብርና ምርቶችን ለማጓጓዝ የሚያስችል የባቡር ሀዲድ ዝርጋታ ሥራ በራስ አቅም ለመዘርጋት ያስችላል ሲሉ ገልፀዋል።
በቀጣይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን የሚያስችል አቅም የተፈተሸበትና ልምድ የተገኘበት ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በጎበኙበት ወቅት የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ