ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ኅልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ኀዘን ገለጹ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፥ እግዚአብሔር በየዘመናቱ አገርን ያለ መካሪ፣ ሕዝብን ያለዘካሪ አይተወውም ብለዋል።
ለዚህም ምስክሩ ታላቅ አረጋዊ ፣ የበሳል አእምሮ ባለቤት፣ አገርን የሚወዱ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ የተጠቁት ወዳጅ፣ የትውልድ አባት የሆኑት የክብር ዶክተር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ነበሩ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ አረጋውያን፣ አፈ ማር ከሆኑ መካሪዎችዋ መካከል አንዱ የሆኑትን፣ ለመወደድ የታደሉትን የዘመናችን ጌጥ ዛሬ አጥታለች ነው ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ።
ይህን የድካም ዓለም መገላገል ለእርሳቸው ረፍት ቢሆንም ለአገር ግን ታላቅ ጉዳት ከመሆኑም በላይ ዕድሜን ከጥበብ ጋር ያዋሐዱ በሁሉ ዘመን አይገኙምና ኀዘናችን ጥልቅ ነው ብለዋል።
ለቤተሰቦቻቸው፣ ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።