የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ የሚያደርግበትን የድህረ-ምርጫ አሠራር ለጋዜጠኞች አስጎበኘ።
የምርጫ ቦርድ ውጤት ማረጋገጫ ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ሽመልስ ሲሳይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሁሉም ምርጫ ክልሎች የማዳመር ሥራ የተጠናቀቀላቸው ሙሉ ሰነዶች በቀጥታ ወደ ዋናው የቦርዱ ውጤት መረከቢያ ክፍል ይገባሉ።
በመቀጠልም በማረጋገጫ ክፍሉ ውስጥ፣ እያንዳንዱ ዕጩ ያገኘው ድምፅ ዋጋ ካላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ እንዲሁም በዕለቱ በአካል ተገኝተው ከፈረሙ መራጮች ቁጥር ጋር መጣጣሙ በጥብቅ ይፈተሻል።
ይህን የማጣራት ሂደት ያለፉ መረጃዎች ተገቢነትና ትክክለኛነታቸውን ወደ ሚያረጋግጠው የኦዲት ቡድን እንደሚመሩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ከዚያም ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ መረጃዎች በቦርዱ የአይሲቲ ሲስተም ውስጥ ገብተው በቦርዱ እንዲጸድቁ ይደረጋል።
በማረጋገጥ ሂደቱ ላይ ያልተጣጣሙና ግድፈት ያለባቸው መረጃዎች ሲገኙ፣ የኦዲት ቡድኑ በሚገባ ከመረመረ በኋላ ለውሳኔ ያቀርባል።