የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ላይ ያጋጠሙ 47 መደበኛ ቅሬታዎችን ተቀብሎ ዝርዝር የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ እና ምርመራው እንደተጠናቀቀ የመጨረሻ ውሳኔውን ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ ምርጫውን ተከትሎ የቀረቡ ቅሬታዎችን፣ በሂደቱ የታዩ ተግዳሮቶችን እና ቦርዱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እየወሰዳቸው ያሉ ፈጣን ምላሾችን በዝርዝር አብራርተዋል።
ቦርዱ በሂደቱ ያጋጠሙ ጥቆማዎችን እና ቅሬታዎችን በኦፕሬሽን ዴስክ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዛቢዎች ዴስክ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በተመሰረተ የጋራ የዋትስአፕ መድረክ እንዲሁም በ7555 እና 6412 አጭር የጥሪ መስመሮች አማካኝነት በንቃት ሲያሰባስብ መቆየቱን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
ቅሬታዎቹ እንደደረሱት ቦርዱ ወዲያውኑ ፈጣንና አስተማማኝ እርምጃዎችን መውሰዱን ያመለከቱት ሰብሳቢዋ፤ የፓርቲ ወኪሎቻቸው የተከለከሉባቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተለይተው በአካል እንዲገቡ መደረጉን፣ በምርጫው ሂደት ጣልቃ የገቡ የአስተዳደር አካላት ከጣቢያዎች እንዲርቁ መደረጉንና የጥሰት ተግባር በፈጸሙ አስፈጻሚዎች ላይ ከሥራ የማሰናበትና ጣቢያዎችን እስከመዝጋት የሚደርስ ጥብቅ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።
የቀረቡትን ቅሬታዎች ሙሉ በሙሉ በሕጋዊ መንገድና በገለልተኝነት ለመዳኘት የሕግ ባለሙያዎች ጉባኤ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ሜላትወርቅ ኃይሉ፥ እስካሁን በፎርም ተሞልተው የቀረቡ 47 መደበኛ ቅሬታዎች በዝርዝር እየተመረመሩ በመሆኑ የዚሁ ማጣራት ሥራ እንደተጠናቀቀ ቦርዱ የመጨረሻ ውሳኔውን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በላሉ ኢታላ