የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከነበረበት የብልሹ አሰራር እና የቴክኖሎጂ ኋላ ቀርነት ወጥቶ፣ የሀገርን ገጽታ በሚመጥን መልኩ ስር ነቀል ሪፎርም እያከናወነ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሯ በኢቢሲ "ስለሀገር" ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቆይታ፤ ተቋሙ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ሲያከናውናቸው የቆዩትን የሪፎርም ስራዎች እና የተመዘገቡ ውጤቶችን አብራርተዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ ተቋሙ ቀደም ሲል የነበረውን ኋላቀር የፓስፖርት አሰራር በማዘመን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የኢትዮጵያን ፀጋዎች የያዘ "ኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት" (e-Passport) ማስተዋወቅም ችሏል።
በተቋሙ የቴክኖሎጂ ሽግግር፤ የሰው ኃይል ግንባታ በማካሄድ፤ የቆዩ አዋጆችና ደንቦች ከወቅቱ የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር እንዲራመዱ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በማድረግ ተከማችቶ የነበረውን ከ350 ሺህ በላይ የፓስፖርት ጥያቄ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ማጠናቀቅ ተችሏል።
ወይዘሮ ሰላማዊት "ኢሚግሬሽን ማለት የሀገር በር ነው። በር ላይ የምታስቀምጠው ሰው ደግሞ ለሀገሩ ታማኝና ለአገልግሎት የተዘጋጀ መሆን አለበት" በማለት፣ በተቋሙ ውስጥ የነበረው 'ሀቀኛ ሰራተኛ የሚበደልበት' ብልሹ አሰራር ተሰብሮ አዲስ የስራ ባሕል መገንባቱን አረጋግጠዋል።
ተቋሙ በመላ ኢትዮጵያ በ22 ቅርንጫፎቹ የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ተገልጋዮች በግማሽ ቀን፣ በሁለት ቀን እና በአምስት ቀን ውስጥ ፓስፖርታቸውን የሚያገኙበት ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱ በቆይታቸው ተመላክቷል።
ተቋሙ እያከናወነ ባለው ስኬታማ ሪፎርም ስራዎች ምክንያት በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተለያዩ ሽልማቶች መታጨቱ ይታወሳል።
በላሉ ኢታላ