Search

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ማስተዋልን እና ትዕግስትን ካስማቸው አድርገው የኖሩ ዕንቁ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡-ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ

ሰኞ ጥቅምት 10, 2018 71

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በሕይወት ዘመናቸው ማስተዋልን እና ትዕግስትን ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ ዕንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ፡፡
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ የአስክሬን ሽኝት ሥነ-ሥርዓት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታየ አፅቀስላሴ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግርም ኢትዮጵያ ዛሬ ታላቅ ሰው በማጣቷ መሪር ኀዘን ውስጥ ናት ብለዋል፡፡
የተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በጎ መምህር እና በጎ አባት እንደነበሩ ገልጸው፤ ለመላው ኢትዮጵያውያን ይህንን እውቀታቸውን ያስተማሩ እንደነበሩም አክለዋል፡፡
በእውቀት ልግስናቸው እና በበጎ ሥራቸው ምንጊዜም ሲታወሱ የሚኖሩ አባት ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በኖሩበት ዘመን ሁሉ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም ሰብከዋል ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝብ ስም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡
በሜሮን ንብረት