Search

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለሰላም እና ለአንድነት ከፊት የቆሙ አባት ነበሩ፡- ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ

ሰኞ ጥቅምት 10, 2018 51

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለኅብረት ከፊት የቆሙ አባት ነበሩ ሲሉ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሐፊ ሊቃ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ከሁሉም ነገር ሰውነትን ያስቀደሙ፣ አብሮነትንና ሰላምን የሚሹ አባት ነበሩ ያሉት ሊቃ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ እርጅና ሳይገድባቸው በሀገራቸው ሰላም እንዲረጋገጥ ቀንና ሌሊት የለፉ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ የማያውቁ ነበሩ ብለዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ተወዳጅና ክብርን የተጎናጸፉ፣ የሀገር አባት፣ የሀገር ዋርካ ስለመሆናቸው የተለያዩ አካላት ምስክርነት ሰጥተዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ "ሰውነት ከእምነት፣ ከዘርም፣ ከሁሉም በላይ ነው" የሚለው ንግግራቸው ዘመን ተሻጋሪና በብዙኀኑ አማኝ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ፣ የዘመኑ ጥቅስ ተደርጎ የሚወሰድና ከሕልፈታቸው በኋላም የሚታወሱበት ድንቅ ንግግራቸው ነው ብለዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ