ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ልማት ለማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከስብሰባው በተጓዳኝ ከአይኤምኤፍ የሞኒተሪ እና የካፒታል ገበያዎች የስራ ክፍል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ እና አይኤምኤፍ መካከል በሞኒተሪ ፖሊሲ፣በካፒታል ገበያዎች እና የፋይናንስ መሰረተ ልማት ጨምሮ በቁልፍ መስኮች ያላቸውን ትብብር እና የቴክኒክ ትስስር ማጠናከርን ያለመ ነው።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ስር የታዩ ለውጦችን ያነሱ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ የማይበገር የፋይናንስ ተቋማት አቅም ለመገንባት፣ አካታችነትን ለማረጋገጥ እና የፋይናንስ መሰረተ ልማትን ለማዘመን የቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የገበያ መረጃ፣ የካፒታል ገበያ ልማት እና የውጭ ምንዛሬ ስርዓትን ማጠናከርን ጨምሮ በጋራ እየተገበሯቸው ያሉ የቴክኒክ ድጋፍ ኢኒሼቲቮችን አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ የሞኒተሪ እና ካፒታል ገበያ ሪፎርሞች፣ የፋይናንስ መረጋጋት እና ኢትዮጵያ ከዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ጋር የበለጠ እንድትተሳሰር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመስራት መስማማታቸው ተመላክቷል።