የአመራር ዕይታ ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ ሃብት ገልጦ እያሳየ መሆኑን የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ወደ ባሌ በተደጋጋሚ ለሥራ መሄዳቸውን የጠቀሱት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ፣ ነገር ግን ባሌን በዚህ መልኩ አይተዋት እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡
"ይህ የሆነው ደግሞ ትላንት የነበራት ተፈጥሮ ስለተቀየረ ሳይሆን ዕይታችን ስለተቀየረ ነው" በማለት ነው አካባቢው ላይ ያለው ሃብት ተደብቆ መኖሩን ያወሱት፡፡
ባሌ ይህንን ሃብት ይዞ በሴፍቲኔት ይኖር ነበር ያሉት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ አሁን ግን ያ የችግር ጊዜ ታሪክ ሆኖ ለሌላውም የሚተርፍበት ልማት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ አመራሮች እና የአሁኑ አመራር ተጣምረው እንደዚህ ዓይነት ልማቶችን ማየታቸው መልዕክቱ ትልቅ እንደሆነም ዋና ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡
"በሦስት ቀናት ጉብኝታችን ባሌን ገልጠን ነው ያየነው" ያሉት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የተጀመሩ ሥራዎች ባሌ ያላትን እምቅ አቅም በተወሰነ መልኩ ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ትላንት ኢትዮጵያ የነበራትን ሃብት ማየት አለመቻላችን የአመራር ዕይታ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ግን ሀገር ያላትን ሃብት ለይቶ ማሳየት የሚችል ራዕይ ያለው አመራር በመምጣቱ ይህ ሃብት መገለጡን አንስተዋል፡፡
መተባበር፣ በጋራ ማሰብ እና በጋራ መሥራት ከተቻለ ኢትዮጵያን ወደ ልዕልና ማድረስ እንደሚቻልም ዋና ፀሐፊው ጠቅሰዋል፡፡
በለሚ ታደሰ