ትውልድ ልመናን እየተቀባበለ መሄድ የለበትም የሚል ፅኑ እምነት ይዘን ፀጋዎቻችንን በማልማት ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር እየሠራን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
"ኢትዮጵያ በባሌ ምድር ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ ይዛ ለምን ለማኝ ሆነች የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልቻልኩም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያን ከኋላ ጋር ያለን ፀብ ወደፊት መራመድ እንዳንችል በእጅጉ ይዞናል፤ ወደኋላ ማየት ያለብን ለትምህርት ብቻ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
ትውልድ ነቅቶ፣ ከመባላት ወጥቶ፣ በባሌ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት አልምቶ ከልመና እንዲወጣ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሳስበዋል፡፡
ሶፍ ኡመርን የመሰለ ሃብት እስካሁን አለመልማቱ ትልቅ ቁጭት እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ብዙ እምቅ ፀጋዎች ያሏት ሀገር ናት ብለዋል፡፡
"ሀገር በአንድ ትውልድ አይሠራም፤ አንድ ትውልድ ጀምሮም አይጨርሰውም፤ ሀገር የሚሰራው በትውልድ ቅብብሎሽ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
በላሉ ኢታላ