የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በህገ ወጥ የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ መንግሥት ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ሀገር ከሚገኙ ሀዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች እና ከንግድ ባንኮች ጋር በትብብር በመስራትና በሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ መንግሥት በርካታ የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ህጋዊ በሆነ መንገድ እየሰሩ በዘላቂነት በቢዝነስ ዘርፉ እንዲቆዩ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
ነገር ግን መንግሥት በተደጋጋሚ ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲገቡ ጥሪ ያደረገላቸውና ጥሪውን ያልተቀበሉ አንዳንድ የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በእነዚህ ህገ ወጥ የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ላይ በጥናት እና በመናበብ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ገንዘብ በነዚህ ሕገ ወጥ ተቋማት በኩል የሚልኩ ዜጎች ከዚህ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል ያሉት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ አንዳንድ አስመጪ እና ላኪ ድርጅቶችም አሁን ላይ የሚወሰደውን ርምጃ አውቀው ሊጠነቀቁ እና ወደ ህጋዊ አሰራር ሊገቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሀገር ደረጃ ሰፊ የውጭ ምንዛሬ ሀብት መኖሩን አንስተው፤ ብሔራዊ ባንክ በአስተማማኝ ሁኔታ ይህን ሀብት እያቀረበ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ለባንኮችም ይሁን ለሀዋላ አስተላላፊ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የሀዋላ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በበኩላቸው፤ ህጋዊ አካሄድን ይዞ ለመንቀሳቀስ እንዲያስችላቸው ከመንግሥት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉትን ዝርዝር ነጥቦች አንስተዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #NationalBank