Search

ኢትዮጵያ እና የቻይናዋ ሻንሺ ግዛት ትብብራቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታወቁ

ማክሰኞ ጥቅምት 11, 2018 61

ኢትዮጵያ እና የቻይናዋ ሻንሺ ግዛት በኢኮኖሚ እና በንግድ ዘርፎች ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ሀገራቱ ይህን ያስታወቁት ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያ እና የቻይናዋ ሻንሺ ግዛት የኢኮኖሚ እና የንግድ ፎረም ላይ ነው።

ሁለቱ ወገኖች በትብብር የሚሠሩት በተለይም በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይሲቲ እና በግብርና እንዲሁም በታዳሽ ኃይል እና በተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ መሆኑ ተነግሯል።

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)፥ ኢትዮጵያ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት የተመቸ እምቅ አቅም እንዳላት አንስተዋል።

በተጨማሪም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ልማትን በማፋጠን ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን አክለዋል።

የሻንሺ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ለኢትዮጵያውያን የሥራ እና የዕውቀት ሽግግር ዕድል ከመፍጠር ባለፈ እነርሱም በሀገሪቱ ካለው ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል እና አማራጭ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የቻይና ሻንሺ ግዛት ምክትል ገዢ ዋንግ ዢኦ በበኩላቸው፥ የግዛቷ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰሳቸው ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የዕውቀት ሽግግርን በማሳለጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ተብሏል።

ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እንዲሁም በቻይና ሻንሺ ግዛት የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመቀየር ረገድም በትብብር ለመሥራት ተነጋግረዋል።

የሻንሺ ግዛት የንግድ ዘርፍ ኃላፊዎች ኢትዮጵያ በተለይ በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች እያከናወነችው ያለውን ሥራ አድንቀው፤ በዘርፎቹ የሁለትዮሽ ትብብር እንዲጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

በብሩክታዊት አስራት

#ebcdotstream #Ethiopia #China #Shaanxi