Search

ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለሰብል ምርምር ስትጠቀም መቆየቷን ያውቁ ኖሯል?

ማክሰኞ ጥቅምት 11, 2018 623

ስለ ኒውክሊየር (አቶሚክ) ኃይል ሲነሳ በአብዛኛው ሰዎች አዕምሮ የሚመጣው አውዳሚ የሆነ የጦር መሳሪያ ነው።

እውነታው ግን ኒውክሊየር ለሰላማዊ አገልግሎት ሲውል ትልቅ የልማት አቅምን የሚያስገኝ የኃይል ምንጭ ነው።

ይህን ኒውክሊየርን ለሰላማዊ አገልግሎት በማዋል ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

ለዚህም ሁነኛ ምሳሌ ሆነው የሚጠቀሱት በተለያዩ ጊዜያት የኒውክሊየር ጨረርን (gamma radiation) በመጠቀም የተሻሻሉት የጤፍ ዝርያዎቿ ናቸው።

ከዓለም አቀፉ የኒውክሊየር ኃይል ኤጀንሲ (IAEA) እና ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO) በተገኘ የቴክኖሎጂ ድጋፍ በቢሾፍቱ የእርሻ ምርምር ተቋም በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በጤፍ ዘር ላይ ምርምር መደረግ ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል።

ይህ ምርምር ለዓመታት ሳይሻሻል የኖረው የጤፍ ዝርያ ያለበትን ድርቅን ያለመቋቋም እና የመጋሸብ ችግር በማስወገድ በሽታን እንዲቋቋም፣ የተሻለ ምርት እንዲሰጥ እና የምግብነት ይዘቱ እንዲዳብር ለማስቻል ያለመ ነው።

ለአብነትም በዚህ የጤፍ ምርምር ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው አንዱ ችግር ቀድሞ የነበሩ የሰብሉ ዝርያዎች ቀጭን እና ረጅም ግንድ የነበራቸው በመሆኑ ትንሽ ንፋስ ወይም ዝናብ ሲመጣ በቀላሉ ይወድቁ ነበር።

ይህ የመጋሸብ ችግር ደግሞ ጤፉ ደርሶ ምርቱን ለመሰብሰብ በሚሞከርበት ወቅት  አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ የምርቱን ብዛት እና ጥራት በመቀነስ ገበሬው ተጠቃሚ እንዳይሆን ያደርግ ነበር።

የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን በማዳቀል እና የኒውክሊየር ጨረርን በመጠቀም ይህን ችግር ለመቅረፍ ለዓመታት በተካሄደው ምርምር የተለያዩ የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን መፍጠር ተችሏል።

ሀገራችን ኒውክሊየርን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል በቅርቡ የጀመረችው እንቅስቃሴ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድግ የሚችል ከመሆኑም በላይ በኃይል ምንጭነት፣ ለሕክምና በጥቅሉም ሀገራዊ ዕድገትን ለማፋጠን የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ ነው።

የኢትዮጵያ የኒውክሊየር መሠረተ ልማት የመገንባት ራዕይ የቴክኖሎጂውን ጠቃሚ ገፅታ በቻ ያማከለ ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ጉልበት የሚፈጥር ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#ebcdotstream #ethiopia #nuclearpower #nucleardevelopment