Search

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሄደችው ርቀት የሚደነቅ ነው - የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ

ረቡዕ ጥቅምት 12, 2018 39

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዓለም የንግድ ድርጅት እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ኒል ቤክ ጋር የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን በተመለከተ ውይይት አካሂደዋል።
በወቅቱም፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢው የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት አስመልክቶ የተካሄደውን የስድስተኛ የሥራ ቡድን ስብሰባ ውጤት እና ከስብሰባው በኋላ የተከናወኑ ቁልፍ ማሻሻያዎችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአባልነት ድርድሩን በማርች 2026 በያውንዴ፣ ካሜሮን በሚካሄደው የዓለም የንግድ ድርጅት 14ኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ ወቅት ለማጠናቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት አስገንዝበዋል።
የአባልነት ሂደቱ የተቀመጠ የጊዜ ገደብን ለማሳካት በሚል ብቻ ላይ የሚመራ አለመሆኑን እና ይልቁንም በተጨባጭ ሥራ፣ በትትርና እና የንግድን መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት አቅምን በሚገነዘብ አመራር መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ለሟሟላት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው በተጨማሪም የገበያ አቅርቦት ላይ እየተደረጉ ያሉ የሁለትዮሽ ድርድሮች የሚገኙበትን ደረጃ እና ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እያገኘች ያለችውን ከፍተኛ ድጋፍ ገልጸው፣ አሜሪካም በተመሳሳይ መልኩ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲኖራት ጠይቀዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተከናወነ ላለው መጠነ ሰፊ ሪፎርም እውቅና እንደሚሰጡ እና የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተኬደውን ርቀት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የተያያዘችውን መንገድ አጠናክራ እንድትቀጥልም ማበረታታቸውም ተመላክቷል።
በተጨማሪም አሜሪካ በቅንነት ተሳትፎ እንደምታደርግ እና ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን እንድታሟላ የሚጠብቁትን መስፈርት በግልፀኝነት ለማሳወቅ ቃል ገብተዋል።