መልካም ታሪኮቻችን ለሀገር ግንባታ መጠቀም እና አንድነትን ተጠቅሞ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ መስፍን ዳኜ ገልጸዋል።
በብሔራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደር ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ የገለፁት አቶ መስፍን፣ ለዘመናት ተዘግቶ በቆየው የባሕር በር ጉዳይ ላይም ትኩረት ሰጥቶ ከነጣይ ትርክት ይልቅ ወደ ወል ትርክት መምጣት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ፖለቲከኞችና ምሁራን ሀገርን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት አንድነትን የሚያረጋግጡ የጋራ ትርክቶችን መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተው፤ ከሚያለያዩን ትርክቶች ይልቅ የሚያስተሳስሩን የጋራ እውነቶችን ማጉላት እና ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ በመሆኑ የትናንት ስህተቶችን እያረሙ ለሀገር የሚመጥን አዲስ ነገር በመፍጠር ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ሀገር ማስተላለፍ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሄለን ተስፋዬ