በወልድያ "ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም" በሚል መሪ መልዕክት ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ተካሂዷል።

በሀገሪቱ የሚታየውን የግጭት አዙሪት ለማስቆም እና ሰላምን ለማምጣት ንግግርን ማስቀደም እንደሚገባ በምክክሩ የተሳተፉት መምህራን ጠቁመዋል።
በዓለማችን ላይ የሚከሰቱ ግጭቶች መቋጫቸው ንግግር መሆኑን በማንሳትም ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በሕዝብ ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ የሚገኘውን ግጭት ለመፍታት፣ ለነገ የሚባል መፍትሔ ሊኖር አይገባም ነው ያሉት ምሁራኑ።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ/ር) የሚታዩ ግጭቶችን ምክንያት እና ውጤት ያማከለ፣ በምርምር የታገዘ የመፍትሄ ሃሳብ ማፍለቅም ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ይጠበቃል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አየለ በበኩላቸው፤ መከላከያ ሠራዊት ሀገር የመጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ታሪክ እና የሚሠራባትን ውጫዊ አሻጥር ምሁራን እንደሚገነዘቡ ገልጸው፤ ምሁራን የባዕዳን ተልዕኮ ያነገቡ ልጆችን መክሮ መመለስ እና የጉዳዩን አሳሳቢነት በሳይንሳዊ ትንታኔ የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸውም ብለዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ፤ ምሁራን ለግጭት ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን በማመላከት እና መንግሥት መሥራት ያለበትን ጉዳይ በማሳየት ግጭትን ከምንጩ እንዲደርቅ መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ ጉዶ በረትና አካባቢው የሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም እጦት ኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንደሚያሳድር ገልጸው፤ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ማጽናት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በመድረኩ በአካባቢው የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በማሠልጠን ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጉ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
ሰላምን ለማስጠበቅ በሚሠራው ሥራም ኅብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ተጠይቋል።