የሕዳሴ ግድብ ስኬት የአሁኑ ትውልድ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ለሚያደርገው ጥረት ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ገለጹ።

በኦሮሚያ ርዕሰመሥተዳድር ጽሕፈት ቤት የሚዘጋጀው ጉሚ በለል 46ኛው የውይይት መድረክ "የሕዳሴ ግድብ ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን" በሚል ርዕስ ተካሂዷል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ደም፣ ላብ እና ዕንባ የተገነባ ነው ያሉት አቶ አወሉ አብዲ፤ የኦሮሞ ህዝብም ከወንድም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራ በመሆን ለግድቡ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስተዋል።
የቀደመው ትውልድ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም፣ የአሁኑ ትውልድ መስዋዕትነት በመክፈል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት እውን አድርጎታል ብለዋል።
በዚህም ግድቡ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን ያደረገ ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን ያሸጋገረ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድ ጥያቄ የሆነውን የባሕር በር ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝም ኢትዮጵያ በታሪክ እና በሕግ ያላትን እውነት ይዛ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ አንስተዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በበኩላቸው፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ለስኬት የበቃ እና የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ያሳየ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ግድቡ መላ ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያቆሙት የሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕህፈት ቤት እና በክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ትብብር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ የሕዳሴ ግድብ ለሀገር እድገት ያለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
በጌታቸው ባልቻ