በ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አስታወቁ።
ሚኒስትሯ እንደገለፁት፤ ባለፉት ሶስት ወራት በጠቅላላው 242 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል።
ከዚህ ውስጥ 74.73 በመቶው የሰብል ምርት ሲሆን፣ 167 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋው ምርት ደግሞ የሆርቲካልቸር (አትክልትና ፍራፍሬ) መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የተሻለ መሆኑንም አንስተዋል።
በዘር የተሸፈነው መሬት በጠቅላላው በዓመቱ 26.32 ሚሊዮን ሔክታር መሬት መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ በሰብል የተሸፈነው 23.76 ሚሊዮን ሄክታር እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመኸር ወቅት በአነስተኛ አርሶ አደሮች የተሸፈነው መሬት 20.3 ሚሊዮን ሔክታር መሆኑን አስታውቀው፤ ይህም ከዕቅድ በላይ የተፈጸመበት ነው ብለዋል።
በተለይም ወሳኝ ከሚባሉት ምርቶች መካከል 4.34 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ 1.52 ሚሊዮን ሄክታር ላይ ሩዝ እንዲሁም በ880 ሺህ ሄክታር ላይ ደግሞ አኩሪ አተር በዘር መሸፈኑን ሚኒስትሯ አክለው ተናግረዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም