በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የተገነቡ የቱሪዝም መዳረሻዎች በርካታ ቱሪስቶችን በምቾት እያስተናገዱ ይገኛል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ባለፉት መቶ ቀናት 376 ሺህ 615 የውጭ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የኮንፈረንስ ቱሪዝም አቅም እያደገ መምጣት ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት መቶ ቀናት ብቻ 29 ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት መቻሉን ገልጸዋል።

በእነዚህ ኮንፈረንሶች ላይም 35 ሺህ 115 የውጭ ሀገር ዜጎች መሳተፋቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ የሀገራት መሪዎች ጭምር የተሳተፉባቸው ሁነቶችም በስኬት መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ኮንፈረንሶችን ማዘጋጀት የሚያስችላትን አቅም መገንባቷን ያሳየ መሆኑን አንስተው፤ ሥራው ከገጽታ ግንባታ ባሻገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የቱሪስት መስህቦችን ለይቶ የማልማት እና ባሉት ላይም እሴት የመጨመር ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም እያደገ መምጣት ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎችንም እየደገፈ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ በሆቴል፣ በትራንስፖርት እና በኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች ላይ እያመጣው ያለው መነቃቃት ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ