የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት) ፓርቲ የምስረታ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው፡፡
ስምረት ፓርቲ በምስረታ ላይ ያለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ሲሆን ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮችና መስራች አባላቱ በተገኙበት ዛሬ የመጀመሪያ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ነው።

የፓርቲው ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጉባዔው መክፈቻ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው የትግራይ ሕዝብ በህወሓት እየደረሰበት ያለውን ጫና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የተመሰረተ ነው፡፡
ፓርቲው ለትግራይ ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በሚሆን መልኩ በአዲስ አስተሳሰብ የተዋቀረ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
የትግራይን ህዝብ ህልውና ለማስጠበቅ መስራት ይኖርብናል ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት ከሌሎች የውጪ አካላት ጋር በመቀናጀት በክልሉ ብሎም በሀገር ሰላም እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ስምረት ፓርቲ እስካሁን ከ5 ሺህ 600 በላይ አባላት መመዝገቡን አመላክተዋል፡፡

ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳዔ በበኩላቸው፤ ስምረት ፓርቲ በኃይል ሳይሆን በሀሳብ ላይ የተመሰረተ ትግል ለማድረግ መመስረቱ የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊነትን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ህወሓት የትግራይን ህዝብ የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገው ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት አቶ መለስ አለም በበኩላቸው፤ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች በትብብር መስራታቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን የፖለቲካ አካሄድ ማሳያ ነው።
ስምረት ፓርቲም ለትግራይ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተሳትፎ አዲስ ሃሳብ ይዞ የመጣ ፓርቲ እንደመሆኑ፣ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ያለው የፖለቲካና የአቋም ልዩነት እንዳለ ሆኖ ሀገሪቱ ለጀመረችው ጉዞ የሚኖረው አበርክቶ የጎላ ነው ብለዋል።
ጉባኤው ከሰዓት በኋላም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።
በዘሃራ መሃመድ