Search

የባሕር በርን ጨምሮ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ስብራቶችን ለመጠገን ከባለድርሻዎች ጋር በትጋት ይሠራል - ብልፅግና ፓርቲ

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 32

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የባሕር በርን ጨምሮ ቀሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ስብራቶችን ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት ይሠራል አለ።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት፥ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች እና የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ መክሮ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ራዕይን ሰንቆ ወደ ተግባር የገባው ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ለህዝብ ቃል የገባውን በውጤታማነት እየፈጸመ ነው ብለዋል።
 
የኢትዮጵያን ቀሪ ስብራቶች ለመጠገን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት እንደሚሠራ ተናግረው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ፓርቲው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በተሠሩ የልማት ሥራዎች ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ውጤት መምጣቱን ገልጸው፤ ለአብነትም ባለፈው ዓመት የ9 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እየተረጋገጠ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው መገምገሙን ጠቅሰው፤ በዚህም ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እና ዘመናዊ አገልግሎት እየተሸጋገረ ይገኛል ብለዋል።
 
በገቢ ማሰባሰብ፣ በወጪ ንግድ እና በተኪ ምርት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በማንሳት፤ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፈጣን ብቻ ሳይሆን አካታች፣ ጥራት ያለው እና የህዝቡን ኑሮ በተጨባጭ እያሻሻለ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በተጀመሩ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸው፤ በሰው ተኮር ሥራዎችም በርካታ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይም ተረጂነትን የማስወገድ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በቂ ፈንድ የመያዝ እንዲሁም ብሔራዊ የመጠባበቂያ ክምችትን በራስ አቅም የማምረት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
 
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሰላም እና የፖለቲካ ጉዳዮችን መገምገሙን በማንሳት፤ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የበኩሉን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።
መጪው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ ግልጽ እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ፓርቲው የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጸዋል።
ውስን የሰላም እና ፀጥታ ችግር የነበረባቸውን አካባቢዎች ለማረጋጋት መንግሥት እና ህዝብ በጋራ በሠሩት ሥራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ጥያቄ ያለው ማንኛውም አካል ጥያቄውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ምህዳር መፈጠሩን ገልጸው፤ ፓርቲው እና የሚመራው መንግሥት ሁልጊዜም በራቸው ለሰላም ክፍት ነው ብለዋል።
በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እና አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የተቀመጠው አቅጣጫ ወደ ተጨባጭ ተግባር መግባቱም ተገምግሟል ነው ያሉት።
በዚህም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋት እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተው፤ እስከአሁንም 16 ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሶብ ማዕከላት የህዝቡ እርካታ ወደ 95 በመቶ መድረሱን ገልጸው፤ ማዕከላቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ 100 ለማድረስ እንዲሠራ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ መንግሥት እና ሀገር ለመገንባት የያዘውን ግብ ለማሳካት የአመራር እና አባላቱን አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ ተግባራትን እንዳከናወነም ገልጸዋል።
አመራርና አባላቱን በተሰጣቸው ተልዕኮ ልክ በየደረጃው የመገምገም ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ በምዘናው መሠረት የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡት እውቅና መሰጠቱን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌላ በኩል የተሰጣቸውን ሀገራዊ እና የፓርቲ ተልዕኮ በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረው፤ ፓርቲው ህዝብ እና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመራችውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።