በኮሪደር ልማት ሥራዎች ድጋፍ ላደረገው መላው የከተማችን ነዋሪ እና በሥራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቀርባለሁ ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ዛሬ በከተማችን በ2ኛው ምዕራፍ ተጀምረው በተጠናቀቁ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ ያደረጉ አካላትን አመስግነናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።
በአራቱ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ማለትም (1) ከመስቀል አደባባይ መገናኛ - ሳዉዝ ጌት፣ (2) ከአንበሳ ጋራዥ - ጎሮ ፣ (3) ከአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል፣ ጎሮ ፣ ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል እንዲሁም ከሳር ቤት - ጀርመን አደባባይ፣ ጋርመንት ፉሪ አደባባይ የኮሪደር ልማት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ ያደረጉ አካላትን አመስግነናል ብለዋል።

በዚህም በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ሌት እና ቀን ሲሰሩ ለነበሩ ከማዕከል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች እና ሰራተኞች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ ማህበራት፣ በጎ ፈቃደኞች እና ሌሎችም ለነበራቸው ከፍተኛ አስተዋፆ እና ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ አመስግነናል ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም መላው የከተማችን ነዋሪ ለሚነዙ ሀሰተኛ አሉባልታዎች ጆሮ ሳይሰጥ፣ የልማት ተነሺ የሆኑትም ያልሆኑትም ለጋራ ልማት በመተባበር፣ ቡና እያፈላ፣ ውኃ እያቀረበ ለልማት ሥራው ውጤታማነት ላሳየዉ ከፍተኛ ድጋፍ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለው ብለዋል።
በ1ኛ እና በ2ኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶች መካከል 342 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ፣ 185 ኪ.ሜ የተሽከርካሪ መንገድ፣ 241 ኪ.ሜ የሳይክል መንገድ ፣ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች፣ በርካታ የሕዝብ መገልገያ እና መዝናኛ ቦታዎች መገንባታቸውን አመላክተዋል።
በተጨማሪ በርካታ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች፣ 101 የሕፃናት መጫወቻዎች፣ 155 የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ 153 ዘመናዊ ፓርኪንግ እና ተርሚናሎች እንዲሁም 210 የሕዝብ መፀዳጃዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ሲሉ ገልፀዋል።