Search

ተፈጥሮ አሟልታ የሰጠችው - የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

እሑድ ጥቅምት 16, 2018 31

ውብ ተፈጥሮን በጉያው የያዘ ምድር ነው፤ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ።

የበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች መገኛ በመሆኑም የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪዎችን ቀልብ ስቧል።

በፓርኩ የሚገኙ ምንጮች ከሀገራችን አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ተስፋን የሚያለመልሙ ወንዞችም መነሻ መሆናቸው ይነገራል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ባሌ ዞን የሚገኘው ብሔራዊ ፓርኩ 2 150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ በአማካይ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ፓርኩ በጥቅጥቅ ደኖች የተሸፈነ፣ ውብ የመሬት ገጽታዎች ያሉት፣ ረግረጋማና እርጥበት አዘል መሬቶችን የያዘ እንዲሁም ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛም ነው።

የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ እጅግ ተወዳጅ ስፍራ መሆኑን በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና የአካባቢ ጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ የሆኑት ደራራ ኩንቡሹ ጉሩሙ ይገልፃሉ።

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መልከዓ ምድር ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያከናወኑት ደራራ ኩንቡሹ ጉሩሙ፤ ፓርኩ ያልታዩ ገፀ በረከቶችን በውስጡ መያዙንም ይናገራሉ።

እጅግ ውብና ማራኪ የሆኑ ፏፏቴዎች፣ ምንጮች፣ ዋሻዎችና ታሪካዊ የትክል ድንጋዮች በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው ይላሉ።

በባሌ ተራሮቹ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ፣ ነገር ግን ገና ያልታዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት፣ ለተለያዩ አገልግሎት መዋል የሚችሉ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች የተመልካችን ቀልብ የሚገዙና ሐሴትን የሚፈጥሩ መሆናቸውንም ተመራማሪው ይገልፃሉ።

አካባቢውን የረገጠ ሰው ስፍራው ምን ያክል ውብ እንደሆነ ይረዳል ይላሉ።

አቶ ደራራ በፓርኩ ዙሪያ ባካሄዱት ጥናትና ምርምር፣ 1980 .. ጀምሮ ባለው ወቅት በአካባቢው ነዋሪዎች ለእርሻ መሬት፣ ለማገዶ እንጨትና ለመሰል ተግባሮች ሲባል፣ በሁሉም አቅጣጫ ፓርኩ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር አስታውሰዋል።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እስካሁን በነበሩ መሪዎች ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን የሚናገሩት አቶ ደራራ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት በፓርኩ ውስጥ የተገነቡ ሎጆች፣ የመንገድና የባቡር መሠረተ ልማቶች፣ ያልታዩ ፀጋዎችን በመግለጥ አካባቢውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ፓርኩን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር እስካሁን ጠብቆ ያቆየው የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት በማግኘቱና በመጎብኘቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረ የሚናገሩት አቶ ደራራ፣ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚያስገኙም አመልክተዋል።

በፊት አስቸጋሪ የነበሩ መንገዶች፣ አሁን በመንግሥት አቅም በመሠራታቸው ቱሪስቶች በቀላሉ የባሌን ተራሮች ጎብኝተው፣ ሶፍ ዑመር ዋሻ ደርሰው ለመመለስ ምቹ ሆኖላቸዋል ይላሉ አቶ ደራራ።

ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ይዘው አርባ ምንጭ ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ እንዲሁም በባሌ ብሔራዊ ፓርክ በመጓዝ ልምድና ተሞክሮ የመቅሰም ልምድ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ደራራ፣ በባሌ ተራሮች ላይ የታየው ዓይነት መልካም ጅምር ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ቢስፋፋ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሀመድ ፊጣሞ