Search

ለአርሶ አደሩ መፍትሔ የሆነው የገጠር ኮሪደር እሳቤ

እሑድ ጥቅምት 16, 2018 34

የኢኮኖሚ ዋርካ የሆነው አርሶ አደር የትላንት ኑሮው ምቹ አልነበረም ይላሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን ነዋሪዎች።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን ያልተመቸ የኑሮ ዘይቤ በመቀየር በጎ ውጤት አምጥቷል ሲሉም ያስረዳሉ።
በተለይም በመልከዓ ምድሯ የተነሳ ለጎርፍ ተጋላጭ የነበረችው በዞኑ የምትገኘው ሲንቢጣ ቀበሌ፣ አሁን ላይ የልማቱ ተቋዳሽ ስለመሆኗም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ "ወደ ውስጣችን እንመልከት፤ አቅማችንን እንፈትሽ" የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እሳቤን ስንተገብር፣ እንደ ችግር ስንቆጥረው የነበረውን ጎርፍ ለምርታማነት ማዋል ችለናል ይላሉ።
በዚህም ከሶስት ጊዜ በላይ ምርት እየተመረተ መሆኑን ጠቁመው፣ ከተረጂነት ወደ ረጂነት በመቀየር ውጤት መመዝገቡንም አስረድተዋል።
ዘመናዊ የገጠር መንደር በአካባቢው ማኅበረሰብ የተለመደውን የሳር ቤት ሞዴልን መነሻ በማድረግ የተገነባ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዘመናዊው የኑሮ ዘይቤ ታግዞ የሚሰራው የአካባቢው አርሶ አደር ለምርትና ምርታማነት ምቹ የሆነውን የአየር ጠባይ እና የአካባቢው መልከዓ ምድር ተጠቅሞ ከቀደመው በበለጠ ተጠቃሚ መሆኑንም የሀላባ ዞን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ወደ ቦታው ያመራው የኢቢሲ "ጉዞ" መሰናዶ፣ አርሶ አደሮች ዘመናዊ መኖሪያ አግኝተው ልጆቻቸውን እያስተማሩ፣ በንብ ማነብና በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ተሰማርተው፣ ዘመናዊ የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ ሆነው፣ በጓሯቸው ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርታማነት ለማሳደግ ሲሰሩ ለመመልከት ችሏል።
 
በአፎሚያ ክበበው