ኢትዮጵያ በውኃ እና ኢነርጂ ዘርፍ ምሳሌ የሚሆን ተግባር እያከናወነች እንደምትገኝ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ ግሬስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውኃ እና ኢነርጂ ሳምንት ከዘላቂ የልማት ግብ እና ከሌሎች ከውኃ፣ ኢነርጂ፣ አካባቢ እና አየር ንብረት ጋር ከተያያዙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ "ውኃ እና ንፁህ ኢነርጂን መጠቀም ለዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም፣ የአረንጓዴ ሽፋን እንዲጨምር እና የካርቦን ልቀት እንዲቀንስ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር የምታከናውናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችል፣ በተፋሰሱ ሀገራት በተሞክሮነት ሊወሰድ የሚገባው እና የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ዕውቅና የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አንስተዋል።
የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ በ1999 የተመሠረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በፍትሃዊ አጠቃቀም እና ተጠቃሚነት ዘላቂ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማረጋገጥ ያለመ እንደሆነ አክለዋል።
በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር፣ ዘላቂ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ፀጥታን የማረጋገጥ ግብን ያነገበ መሆኑንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የ2ኛው የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሳምንት መሪ ሃሳብ፣ ኢኒቬቲቩ የያዘውን ግብ ወደ ሀገራዊ ተግባር ከመቀየር ጋር የተሰናሰለ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።
በናይል ተፋሰስ የውኃ ሀብት ላይ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ድንበር ዘለል ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
#EBCdotstream #water #energy #nilebasininitiative #nbi