በኮሪደር ልማት አማካኝነት በመንገድ ዳር የተገነቡ ንፁ መፀዳጃ ቤቶች እና ማረፊያ ስፍራዎች ለበርካታ አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ውጤታማ መሆናቸው ይገለፃል። 
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ጉጆ፣ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ለአካል ጉዳተኞችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ምቹ የመፀዳጃ ቤት እና የመታጠቢያ ቤት እጥረት እንደነበረባቸው ገልጸው፣ የኮሪደር ልማቱ ይህንን ችግር መፍታት ያስቻለ ጅምር ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በተሠራው የኮሪደር ልማት አንድ አካል ጉዳተኛ በዊልቸር ከቦሌ እስከ ፒያሳ ያለምንም እንቅፋት ደርሶ መመለስ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ይህ ቀላል ለውጥ አይደለም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በከተማዋ የነበሩ የታክሲ ፌርማታዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ባለመሆናቸው አስቸጋሪ እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ግን ተደራሽነትን በአሟላ መልኩ በዘመናዊ መንገድ መሠራታቸው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምባቸው ሆነዋል ሲሉ አስረድተዋል።
አካል ጉዳተኞች ዊልቸር በመጠቀም በዘመናዊ መልክ በተገነቡ የታክሲ ፌርማዎች ላይ በተሻለ ሁኔታ አገልግሎት እያገኙ መሆኑንም አንስተዋል።

የኮሪደር ልማት የከተማዋን መሠረተ ልማት በማዘመን የአካል ጉዳተኞችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ በመመለስ ረገድ ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረገ ትልቅ ዕሳቤ ይዞ የመጣ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
የልማት ሥራዎች ከመጀመራቸው በፊት አካል ጉዳተኞችን ማማከርና በአፈጻጸም ዙሪያ ኅብረት መፍጠር ከተቻለ የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል የኮሪደር ልማቱ አመላካች መሆኑን አንስተዋል።
የኮሪደር ልማቱ የብስክሌት መንገዶችን፣ የእግረኞች መንገዶችን፣ የታክሲ ፌርማታዎችንና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ሲሆን፣ ለሁሉም ሰው ክብር በሚሰጥ መንገድ በስፋት ታስቦ የተሠራ ነው ብለዋል።
እስካሁን የተሠራው ሥራ ከጠበቅኩት በላይ ነው ያሉት መሆኑን ገልጸው፣ ወደፊትም የተጀመሩ በጎ ሥራዎችን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል አካቶ የተጀመረው ሥራ በሁሉም የክልል ከተሞች በሚሠሩ የኮሪደር ልማቶች የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            