በኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም የአካል ጉዳተኞች ለግል አገልግሎት ብቻ የሚውሉ ልዩ ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ እና ታክስ ነፃ ከውጭ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ መመሪያ ቁጥር 41/2007 ወጥቶ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
መመሪያው ማንኛውም አካል ጉዳተኛ ራሱ የሚጠቀምበትን ተሽከርካሪ ከቀረጥ እና ታክስ ነፃ አስገብቶ እንዲጠቀም የሚያስችለው ነው።
አዲስ የተሻሻለው መመሪያ ደግሞ አካል ጉዳተኞች ራሳቸው መንዳት እንደማይችሉ በሕክምና ከተረጋገጠ በሹፌራቸው መጠቀም እንዲችሉ ይፈቅዳል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ዓባይነህ ጉጆ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንዳሉት፥ አካል ጉዳተኞች በራሳቸውም ሆነ በሌላ ሰው አሽከርካሪነት እንዲጠቀሙ በሚፈቅደው መመሪያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ6 ሺህ በላይ አካል ጉዳተኞች ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥ እና ታክስ ነፃ ከውጪ ማስገባት ችለዋል።
በዚህም መንግሥት በአንድ መኪና ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ቀረጥ በማንሳት አካል ጉዳተኞች መኪና አስገብተው እንዲጠቀሙ አስችሏል፣ ይህም የመንግሥትን ትልቅ ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
ማንኛውም አካል ጉዳተኛ አቅም ካለው አዲስ በተሻሻለው መመሪያ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ነው ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዓባይነህ ጉጆ ያስታወቁት።

በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመኑን እና ተጠቃሚዎቹም አገልግሎቱን በኦንላይን እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ብዙ ውጣ ውረድ እንደነበረው አስታውሰው፤ አሁን አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ እንግልቱን ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል።
አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሁሉ ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም ሚኒስትር ዴኤታዋ አረጋግጠዋል።
በላሉ ኢታላ
#ebcdotstream #ethiopia #feapd #mowsa #specialneeds #differentlyabled