Search

የያዙት ቁልፍ እና መጠቀሚያ ዕቃ ከየት እንደተገኙና ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ ማስረዳት ካልቻሉ እንደሚጠየቁ ያውቃሉ?

ቅዳሜ ጥቅምት 22, 2018 42

ሰዎች ሕግን ባለማወቅ ወይም ባለመረዳት የተነሳ በሕግ ሲጠየቁ ይስተዋላል። የሕግ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ግን ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት አያድንም።
የሕግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑት አርባ በየነ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ አጠራጣሪ የሆኑ ነገሮችን ይዞ መገኘት በሕግ ፊት ተጠያቂ ያደርጋል ይላሉ።
የተለያዩ ቁልፎችና የቁልፍ ማንጠልጠያዎችን፣ ጉጠቶችን እና የተለያዩ መገልገያ መሣሪያዎችን እንዲሁም ዋጋ ያላቸውን ሰነዶችን ይዞ የተገኘ እና ከየት እንዳመጣቸው እንዲሁም ለምን አላማ እንደሚውሉ በአግባቡ ማስረዳት ያልቻለ ሰው በሕግ እንደሚጠየቅም አስረድተዋል።
የተለያዩ መሣሪያዎችን ይዞ መገኘቱ ሳይሆን መሣሪያዎቹን ለምን ዓላማ እንደሚጠቀምበትና ከየት እንዳመጣቸው ማስረዳት ያልቻለ ሰው ከ15 ቀን ባልበለጠ እስራት እንዲሁም በገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣም ገልጸዋል።
በየመንገዱ ብዙ ቁልፎችን አንጠልጥለው የሚሄዱ ሰዎችን መመልከት የተለመደ ቢሆንም፣ እነዚህ ቁሶች የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈጸም የሚያግዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ በሕግ አግባብ እንደሚታዩ ጠበቃው ተናግረዋል።
ሕጉ መቀጮን ሲደነግግ የራሱ ዓላማ እንዳለው ያነሱት ጠበቃው፤ ይህም ወንጀልን ለመከላከል ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለማወቅም ሆነ በቸልተኝነት የሚፈጸሙ ድርጊቶች በሕግ ፊት ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት